GridArt_20260615_154808026

​በድንገተኛ የእሳት አደጋ ሳቢያ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት የነበረውን የኦቶና ሆስፒታልን ዳግም ለመገንባት የሚያስችሉ የቅድመ-ሥራ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን ሂደቱን በቅርብ የሚከታተሉ የውስጥ ምንጮች ለ WT Media ገልጸዋል።

​ከግንባታው ቅድመ-እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከተገኙ ታማኝ ምንጮች የተረጋገጡት ዋና ዋና ዝርዝር መረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
​
ምንም እንኳን የህንፃ ግንባታ የማስፈቀዱ መዋቅራዊ ሂደት እጅግ የዘገየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋዊ ፈቃድና በጀት ተሰጥቷል።

​በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ በ3000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍ እና 6 ወለል (G+5) ያለው አዲስ ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ ተጠናቀዋል።

​የእሳት አደጋ የደረሰበት የቀድሞው አሮጌ ሕንፃ ታሪካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ አይፈርስም። በምትኩ ጥገና ተደርጎለትና ጣሪያ እንዲለብስ ተደርጎ ለቀለል ያሉ የሕክምና አገልግሎቶችና ለተለያዩ የቢሮ ሥራዎች እንዲያገለግል ለማድረግ ታቅዷል።
​
​ግንባታው በተጨባጭ መሬት ላይ መቼ ይጀምራል? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ በቅድመ-ሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘው አካል ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባራዊ የግንባታ ምዕራፍ እንደሚገባ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

​የኦቶና ሆስፒታል መውደም ላለፈው አንድ ዓመት በአካባቢው የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖና ሰብዓዊ ቀውስ ማሳደሩ የሚታወስ ሲሆን የተጠቀሰው የአንድ ወር ጊዜ አጭር በመሆኑ የተገቡት ተቋማዊ ቃላቶች መሬት ላይ በተግባር መተርጎማቸውን WT Media በቅርብ እየተከታተለ መረጃዎችን የሚያደርስ ይሆናል።