GridArt_20260216_201221613

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን በሚገኘው ዘይሴ ብሔረሰብ ላይ የተከፈተው መጠነ-ሰፊ ጥቃት ወደ አስከፊ ደረጃ መሸጋገሩንና ዛሬ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም በደንብሌ ቀበሌ ብቻ ከ20 በላይ ንጹሐን ዜጎች በጸጥታ ኃይሎች መረሸናቸውን ለ WT Media የደረሱ አስቸኳይ መረጃዎች አመልክቷል።

ድርጊቱ “በአከባቢው መንግሥት የታገዘ “የዘር ማጥፋት ዘመቻ” ሲሉ ነዋሪዎችና የዐይን እማኞች በከፍተኛ እሮሮ ድምፅ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ዛሬ ማምሻውን ከስፍራው ለ WT Media በስልክና በማስረጃ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የክልሉ ጸጥታ አካላትና የጋሞ ዞን መዋቅር በዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ ከ20 በላይ ሰዎችን ከየቤታቸው እየጎተቱ በማውጣት በጥይት ረሽነዋል።

የተረሸኑት ዜጎች አስክሬን በደንብሌ ጤና ጣቢያ በካንፋቸው (በአንድ ላይ) በሚያሳዝን ሁኔታ ተከማችቶ እንደሚገኝና የአካባቢው ማኅበረሰብ በታላቅ ድንጋጤና ስቃይ ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

በዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ ደግሞ ከ60 በላይ የሚሆኑ ወንዶችና ወጣቶች ከየቤታቸው ተለቅመው በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ሲሆን፣ እስካሁን የት እንደደረሱና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አይታወቅም።

ከትናንት ከቀኑ 12:00 ሰዓት ጀምሮ የተከፈተው ጥቃት በምሽትም ቀጥሎ ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል ሲሉ የአከባቢው ምንጮች ለ WT Media አስረድተዋል።

ዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ ዛሬ ወደ አመሻሽ ገፅታ

በአሁኑ ሰዓት በዘይሴ አካባቢ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የከባድ መሣሪያና የጥይት ተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑንና ጦርነቱ ነገም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

ይህ አሰቃቂ ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረገው፣ የዘይሴ ብሔረሰብ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እያቀረበ ያለው  “ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር” የሚለው ሕገ-መንግሥታዊ የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን አመራሮች፣ ይህንን ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ በሥልጣን ሽፋን በማፈን፣ ጥያቄውን የሚያነሱ ዜጎችን በማሳደድ፣ በማሰርና በመግደል ላይ እንደሚገኙ WT Media ቀደም ሲል ባደረጋቸው የምርመራ ዘገባዎች ማረጋገጡ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት የተከፈተው ጦርነት “ምርጫን ለማደናቀፍ” ታስቦ በጋሞ ዞን አመራሮች በተሰጠ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚፈጸም መሆኑ ተመልክቷል።

አንድ በስፍራው የሚገኝ የብሔረሰቡ ተወላጅ በለቅሶ የታጀበ ቃሉን ለ WT Media እንዲህ ሰጥቷል፦ “ጭፍጨፋው አልቆመም! ዛሬ ብቻ ከተረሸኑት 20 ሰዎች ጋር ቁጥሩ 25 ደርሷል። ወጣቶቻችንን ከየቤታቸው እያፈሱ ወስደው የት እንዳደረጓቸው አናውቅም። መንግሥት በገዛ ሕዝቡ ላይ ጦርነት ከፍቷል። እባካችሁ ድምፅ ሁኑልን፣ እያለቅን ነው!”

በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ግልጽ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና “የዘር ማጥፋት ዘመቻ” በመሆኑ፦ የፌዴራል መንግሥትና ለመከላከያ ሠራዊት፦ በክልሉ ጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸመውን ንጹሐን የማረሽን ተግባር በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት እንዲያስቆሙ፤

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች (Amnesty, Human Rights Watch)፦ በዘይሴ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ በገለልተኛ አካል እንዲመረምሩና ድምፅ እንዲሆኑ፤ ኢሰመኮ ደግሞ፦ በአካባቢው ያሉ እስረኞችና የታፈኑ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲጣራ እንጠይቃለን።

WT Media በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ የሚፈጸመውን ይህን ታሪካዊ በደል እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ በቅርበት መከታተሉንና አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media